Ethiopia Ethiopian News

Sport: የዩክሬይን ፖለቲካና እግርኳስ

ራሺያ የ2018ቱ የዓለም ዋንጫ አዘጋጅ ሀገር ናት፡፡ የፊፋ አባል የሆነችውን የዩክሬይንን ሉዓላዊ ግዛት በኋይል የያዘችው ሀገር ዓለምአቀፉ የእግርኳስ ውድድርን ልታዘጋጅ እንደማይገባት በመናገር ፕሬዝዳንቷ ቭላዲሚር ፑቲን አቋማቸውን መለስ ብለው እንዲመረምሩ ለማድረግ የሚሞክሩ ወገኖች አሉ፡፡ የእግርኳስ ባለስልጣናት ግን ይህን መሰሉን ንትርክ መስማትን አይፈልጉም፡፡ ‹‹ስፖርትና ፖለቲካ ተለያይተው መታየት ይገባቸዋል›› በሚለው አቋማቸው መፅናትን ይመርጣሉ፡፡ የቤላሩስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርም እንደ ፊፋ እና የአውሮፓ እግርኳስ ማህበር ባለስልጣናት ሁሉ ስፖርትና ፖለቲካ በተለያዩ አይነቶች መታየት እንደሚገባቸው ተናግረዋል፡፡ እውን እግርኳስና ፖለቲካ ሊነጣጠሉ ይችላሉ?
putin
በአንዳንድ እግርኳስ ክለቦች ውስጥ እግርኳስና ፖለቲካ ተነጣጥለው ይታያሉ፡፡ የጀርመኑ ሼልክ 04 አንዱ ተጠቃሽ ነው፡፡ በሩህር ከተማ በሚገኙ ኩሩ ላብ አደሮች የሚደገፈው ክለብ በእነዚህ ደጋፊዎቹ ባለቤትነት በፍፁም ዴሞክራሲያዊ መርሆዎችና በማህበረሰብ ደንቦች ይመራል፡፡ ደጋፊዎች በክለቡ ዕጣ ፈንታ ላይ የመወሰን ድምፅ አላቸው፡፡ በተወሰነ ደረጃም በፖሊሲዎች ላይ ለውጥ የማድረግ ስልጣን አላቸው፡፡ ለምሳሌ፡- ባለፈው ዓመት የኢንተርኔት የቲኬት ሻጭ ከሆነው ኩባንያ (ቪያሳጎ) ጋር ክለቡ የፈጠረውን አወዛጋቢ ትብብር መልሶ እንዲያጤነው አስገድደውታል፡፡ የሼልክ ፕሬዝዳንት ከሌመንስ ቶኒስ ከራሺያው ፕሬዝዳንት ፑቲን ጋር እጅግ የጠበቀ ግንኙነት እንዳላቸው ይታወቃል፡፡ የማሊያ ላይ ስፖንሰር Gazprom ፑቲን የሚመሩት የራሺያ መንግስት በባለቤትነት የያዘው የኢነርጂ ኩባንያ ሲሆን ለጀርመኑ ክለብ በዓመት 16 ሚሊዮን ዩሮ ይከፍላል፡፡
Gazprom የራሺያው ክለብ ዜኒት ሴንት ፒተርስበርግ አብላጫ ባለድርሻ መሆኑም ይታወቃል፡፡ ፕሬዝዳንት ፑቲንና ጠቅላይ ሚኒስትር ዲሚትሪ ሜድቨዴቭ ደግሞ የዜኒት ደጋፊ ብቻ ሳይሆኑ በኮሚዩኒስቶቹ ዘመን ሌኒንግራድ ተብላ ትጠራ የነበረው የሴንት ፒተርስበርግ ከተማ ተወላጆች ናቸው፡፡ ፑቲን በሀገራቸው ክለብ ላይ ያላቸው ቀጥተኛ ተፅዕኖ ሰሞኑን ከዩክሬይን ጋር በፈጠሩት የፖለቲካ ትኩሳት ፈተና አይገጥመውም፡፡ ሆኖም የሼልክን የመሰለው ድንበር ዘለል እግርኳሳዊ ግንኙነታቸው ላይ ፖለቲካዊ እርምጃዎች ጥላ አያጠላም ማለት አይቻልም፡፡
ፑቲን የክሬሚያን ባህር ገብ ግዛት በወታደሮቻቸው ቁጥጥር ስር በማድረጋቸው ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጫናዎች እየደረሰባቸው መሆኑ ይታወቃል፡፡ አንዳንድ የሼልክ ደጋፊዎችም ባላቸው የመወሰን መብት በመጠቀም ክለባቸው ከፑቲን ጋር ያለውን ግንኙነት እንዲያቋርጥ እየጠየቁ ይገኛሉ፡፡
ደጋፊዎቹ በሚያሳትሙት ‹‹Schalke unser›› በተሰኘው መፅሔትም የክለቡን ቦርድ ራሱን ከፑቲን እንዲያርቅ የሚጠይቁ ይፋዊ ደብዳቤ መላኩ ታውቋል፡፡

‹‹ሼልክ እግርኳስ ክለብ ዴሞክራሲያዊ መሰረት ያለው ክለብ ነው፡፡ ሀሳብን የመግለፅ ነፃነትንም በከፍተኛ ደረጃ ያከብራል›› ይላል በመፅሔቱ ላይ አስተያየቱን ያሰፈረው ሮማን ኮልበ፡፡ ‹‹እናም (እንደ ፑቲን ያለውን) አምባገነን ማገልገል የለብንም›› ሲል ያክላል፡፡ በደብዳቤውም ላይ ይኸው መልእክት በግልፅ ሰፍሯል፡፡ ደብዳቤው በክሬሚያ ባህር ገብ ምድር በተፈጠረው የፖለቲካ ቀውስ ብቻ ሳይሆን ፕሬዝዳንት ፑቲን ፖለቲካ እና ስፖርት መለያየት እንደሚገባቸው በተግባር ለማሳየት ሲሉ ከሼልክ ቡድን አባላት ለመገናኘት ግብዣ ለማቅረባቸው የተሰጠ መልስም ነው፡፡ ግብዣውን ከላኩበት ሰዓት ብዙም ሳይቆይ ወታደሮቻቸውን ወደ ክሬሚያ እንዲገቡ አዝዘዋል፡፡

ፑቲን ከክሬሚያ ጋር በተያያዘ የተለያዩ ተፅዕኖዎች እየተደረጉባቸው ባለበት በዚህ ሰዓትም ቢሆን ግብዣውን አልሰረዙም፡፡ ደጋፊዎች ክለባቸው ግብዣውን እንዳይቀበል በጠየቁበት ባለፈው ሳምንት የሼልክ ጄኔራል ማናጀር ሆርስት ሄሉድት ቡድኑ ወደ ሞስኮው የመሄድ ምንም አይነት እቅድ እንደሌለው ባዘጋጁት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ አስታውቀዋል፡፡

የጉዞ ዕቅድ አለመያዙ ብዙዎችን የሼልክ ደጋፊዎች እፎይ የሚያሰኝ ነው፡፡ ዓለም ፑቲን ላይ ጫናውን በጨመረበት ወቅት ላይ ዩሊያ ድራክስሰር፣ ክላስ ያንሁንቴላር እና ኬቨን ፕሪንስ ቦአቴንግን የመሳሰሉት ተጨዋቾች ፕሬዝዳንቱን ለመጎብኘት ቢሄዱ እጅግ አሳፋሪ ይሆን ነበር፡፡ ኦፊሴላዊው ጉብኝት ባይኖር እንኳን የሼልክ እና የፑቲን ግንኙነት ጠንካራ መሆኑን አሁንም እንደቀጠለ ነው፡፡ የሼልክ ሊቀመንበር ክሌመንስ ቶኒስ ከፕሬዝዳንቱ ጋር የቀረበ የግል ወዳጅነትም አላቸው፡፡
ባለፈው ጃንዋሪ ቶኒስ ክለቡን በራሳቸው ዕቅድ ከዕዳ ነፃ እንደሚያደርጉት ቃል ገብተው ነበር፡፡ በስጋ ንግድ የታወቁት እኚሁ ቱጃር ባለፉት ሁለት ዓመታት ብቻ የሼልክን ዕዳ በ50 ሚሊዮን ዩሮ እንዲቀንስ አድርገዋል፡፡ ክለቡ አሁንም 170 ሚሊዮን ዩሮ ዕዳ ተሸክሟል፡፡ ስለዚህ ሼልክ ከዕዳ ነፃ የመሆን እቅዱን ተግባራዊ ለማድረግ Gazprom ያስፈልገዋል፡፡ የስፖንሰሮቹ ስምምነትም በቅርቡ እስከ 2017 ድረስ ተራዝሟል፡፡ ሼልክ እንዳለፈባቸው ፈተናዎችና እንደ ቀድሞ አሰልጣኙ ፌሊክስ ማጋት የተጨዋቾች ግዢ ፖሊሲ ዕዳው ከዚህ በላይ በናረ ነበር፡፡ Gazprom ከጎኑ መኖሩ ከተባባሰ የፋይናንስ ቀውስ እንዲድን አስችሎታል፡፡ ይህም ሊቀመንበር ቶኒስ ከፕሬዝዳንት ፑቲን ጋር ባላቸው ቅርበት የተወሰነ ጉዳይ መሆኑ አያጠራጥርም፡፡

ሊቀመንበሩም ሆኑ የክለቡ ባለስልጣናት የራሺያው ኩባንያ ጋር ባላቸው ግንኙነት መጠቀማቸውን ስለሚያውቁ ራሳቸውን ከፒቱን ለማራቅ አልወሰኑም፡፡ እንዲያውም ክለቡ ለሱዶቼ ዜይቱንግ ጋዜጣ በሰጠው መግለጫ ከ Gazprom ጋር ያላቸው ግንኙነት ‹‹የታመነና ገንቢ›› መሆኑን አስታውቋል፡፡ ቶኒስ ስለ ፑቲን ጉዳይ ሳይናገሩ አልቀሩም፡፡ ክለባቸውም ግንኙነቱን ከኩባንያው ጋር ብቻ እንዲሆን በመገደብ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ማስታወቁን በመምረጥ ማንም ሰው ጥርጣሬ ውስጥ እንዳይገባ ለማድረግ ሞክረዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ቶኒስ ባደረጓቸው የተለያዩ ቃለ ምልልሶች ላይ ከፕሬዝዳንት ፑቲን ጋር በተገናኙ ቁጥር ሁለት ነገሮችን በስጦታ መልክ እንደሚያበረክቱላቸው ተናግረዋል፡፡ የሚያመርቱትን ስጋ ናሙና እና ሼልከን ማሊያ መሆኑ ነው፡፡ በ2012 በኮሎኝ ከተማ ከሚታተመው ‹‹ኤክስፕረስ›› ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቆይታ ቶኒስ ፑቲንን ‹‹ደስታን አብረው ሊካፈሏቸው የሚመቹ ሰው›› ሲሉ ገልፀዋቸው ነበር፡፡ አክለውም ‹‹በጣም ጥሩ ምግብ አብሳይ እና አንዳንድ ጊዜም ማሳቅን የሚወዱ›› መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ በፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ፑቲን ስላላቸው አመርቂ ያልሆነ ሪከርድ ሲጠየቁም የሼልከው ሊቀመንበር ንፅፅራዊ መልስ መስጠትን መርጠዋል፡፡ ‹‹የራሺያንና የጀርመንን ዴሞክራሲዎችን ማወዳደር አይቻልም›› ካሉ በኋላ በፑቲን አመራር ስር በራሺያ ብዙ ነገሮች በአዎንታዊ ዕድገት ማሳየታቸውን ጠቅሰዋል፡፡

የሰሞኑ የክሬሚያ ቀውስ እስኪነሳ ድረስ ፑቲንን ማሞገስ በሼልክ መጥፎ አልነበረም፡፡ አሁን ግን ነገሮች ተቀይረዋል፡፡ ደጋፊዎች ተቆጥተዋል፡፡ የደጋፊዎቹን መፅሔት የሚያዘጋጀው ሮማን ኮልበ እንደሚናገረው የሼልክ ወዳጆች ቡድን ከፑቲን ጋር እንዲገናኙ ፈፅሞ አይፈልጉም፡፡ ‹‹በቅርቡም ፒቱንና ጋዝፕሮምን የሚቃወሙ የጨረቃ ላይ ፅሑፎች በስታዲየሙ ውስጥ ብንመለከት አልገረምም›› ብሏል፡፡

በዚህ መልኩ ተቃውሞን ማሰማት ምን ያህል ውጤታማ እንደሆነ ለማየት ጊዜ ያስፈልገናል፡፡ ሆኖም ስፖርትና ፖለቲካ እርስ በርሳቸው ለመተሳሰራቸው የሼልክ እና የፑቲን ጉዳይ ጥሩ ማስረጃ ነው፡፡ ሼል ከራሺያ ጋር ባለው ስራ ግንኙነት እጅጉን መጠቀሙ የሚክድ የለም፡፡ ይህም በተወሰነ መልኩም ከራሺያ ጋር አቆራኝቶታል፡፡ Gazprom የዓለማችን ግዙፍ የተፈጥሮ ጋዝ አምራችና አቅራቢ ሲሆን ከፕላኔታችን ታላላቅ ኩባንያዎች አንዱ ነው፡፡ ቃሉ ‹‹የጋዝ ኢንዱስትሪ›› የሚል ትርጉም ይሰጣል፡፡ በ2011 ብቻ 513.2 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትርስ የተፈጥሮ ጋዝ አምርቷል፡፡ በዚያው ዓመት ራሺያ ከዓመታዊ ገቢ 8 በመቶ ያህሉን ያገኘችው ከጋዝፕሮም ንግድ ነው፡፡ በ2012 ደግሞ 153 ሚሊዮን ዶላር ገቢ አስመዝግቧል፡፡ 35 ሺ ሰራተኞች ካሉት ከዚህ ተቋም ጋር ክለባቸው ያለው ግንኙነት እንዳይቋረጥ የሚፈልጉ ደጋፊዎች ቁጥር ጥቂት እንደማይሆን እርግጥ ነው፡፡ ሆኖም ከፑቲንና ከጋዝፕሮም ጋር የክለባቸው ስም አብሮ በመጠራቱ ቅር የሚሰኙ መብዛታቸው አያጠራጥርም፡፡ የሼልክን እግርኳሳዊ ውርስ እሴቶቹን ያቆሽሻል የሚል እምነት ያሳድርባቸዋል፡፡ ከጊልሴንኪርችን ከተማ ውጭም ይዘላል፡፡

በሀገሪቱ ትልቁ የክለቦች ውድድር ዋና ዋና ስፖንሰሮች አንዱ ለመሆን ከአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር ጋር በመስማማቱ ጋዝፕሮም በጨዋታዎች ላይ በሜዳው ዙሪያ ባለው የማስታወቂያ ሰሌዳ ላይ በጉልህ ይታያል፡፡ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግም ከቼልሲ እግርኳስ ክለብ አበይት ፓርትነሮች አንዱ ነው፡፡ የክሬሚያን ቀውስ ከራሺያ መንግስት እና ቭላዲሚር ፑቲን እንዲሁ አይነጣጠሉም፡፡ የራሺያ መንግስት ኩባንያ የሆነውና ፑቲን በቀጥታ የሚያዙበት ከጋዝፕሮም ጋር ግንኙነቱን የጠበቀ በተለይ የምዕራብ አውሮፓ ሀገር ክለብ ደግሞ ከሞራል ጥያቄዎች የማይሸሽበት ጊዜ ላይ እንገኛለን፡፡ ፖለቲካና ስፖርትም የማይነጣጠሉበት ዘመን ላይ ደርሰናል፡፡

Ze-Habesha Website may contain advice, opinions, and statements of various information and content providers. The Website neither represents nor endorses the accuracy of information or endorses the contents provided by external sources. All blog posts and comments are the opinion of the authors.

Print Friendly

Source Article from http://www.zehabesha.com/amharic/archives/13834

Post Comment