[ሚኒሶታው መድሃኔዓለም ቤ/ክ ጉዳይ] “ለቤተክርስቲያናችን ሰላምና አንድነት ስንል ዝም አንልም” – ለቤ/ክ ሰላምና አንድነት ከቆሙ ምዕመናን

debereselam Minnesota
3/19/2014
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሃዱ አምላክ፤ አሜን !

ለቤተክርስቲያናችን ሰላምና አንድነት ስንል ዝም አንልም።
ለቤተክርስቲያን ሰላምና አንድነት ከቆሙ ምዕመናን።

ቤተክርስቲያናችን ደብረሰላም መድኃኔዓለም በይፋ ከተምሠረተችበት ከ 1994 ዓ.ም እ.ኤ.አ ጀምሮ በብዙህ ሺህ ለሚቆጠሩ ስደተኛ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች እጅግ በርካታ መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎቶችን ስትሰጥ ቆይታለች፤አሁንም በመስጠት ላይ ትገኛለች። የቤተክርስቲያን ሕይወትና ጉዞ ግን ቀላልና አልጋ በአልጋ ስላልሆነ በየጊዜው ብዙ ፈተናዎች ያጋጥማሉ። የዚህ የዛሬው መልዕክት ዋና አላማም በቤትክርስቲያናችን ጉዞ ውስጥ አንዱና ትልቁ የሆነውን በአሁኑ ሰዓት ያጋጠመንን ፈተና ከሥር ከመሠረቱ ለሁሉም ለማሳወቅ ነው።

ሁላችሁም እንደምታውቁት ቤተክርስቲያናችን ደብረሰላም ፍጹም የኦርቶዶክ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን እምነት፣ ቀኖና፣ትምሕርትና ትውፊት የሚፈጸምባት ብቻ ሳትሆን የሚሰጠው አገልግሎትም በኢትዮጵያ ካሉ ታላላቅ አድባራትና ገዳማት ጋር የሚተካከልና ዝናዋም በመላው ዓለም የገነነ ነው። ይህች ቤተክርስቲያን ገና ሥትመሰረት ጀምሮ በገለልተኛ አስተዳደር እንድትመራ በወቅቱ የነበሩ መሥራች አባላት ተስማምተው ያደረጉት እንደሆነ ሁሉም የሚመሰክሩት ነው። ይህም የሆነበት ዋናው ምክንያት በወቅቱ በሥልጣን ላይ የነበሩት ፓትርያርክ በመንግሥት ጣልቃ ገብነት ተነስተዋል በሚልና የተሾሙትም አባት የመንግሥት ብርቱ ደጋፊ እንደነበሩ ይነገር ስለነበረ በተጨማሪም በምዕራቡ ዓለም ለረጅም ጊዜ የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ ክ ሊቀ ጳጳስ ሆነው ያገለገሉት አባት (አቡነ ይስሐቅ) የፕትርክና ሹም ሽሩን ድርጊት በመቃወማቸው ቤተክርስቲያኗ ከየትኛውም አስተዳደር ሳትወግን በአስተዳደር ገለልተኛ ሆና በሜኖሶታ የቤተክርስቲያናት ማቋቋሚያ ሕግ እንድትተዳደርና ለውስጥ አሰራርም መተዳደሪያ ደንብ እንዲዘጋጅ ተደርጓል።

በተግባርና በመረጃ እንደታየውም በኢትዮጵያ በሥልጣን ላይ የተቀመጡት አባት በርግጥም የመንግሥት ጉዳይ አስፈጻሚ እንጂ ለቤተክርስቲያንና ለምእመናንን ብዙም ደንታ የነበራችው ስላልነበሩ፤ ከስልጣን የተባረሩት አባትም በወቅቱ እንደተባለው በህመም አለመሆኑና በመንግሥት ትእዛዝ እንደተነሱ መረጃዎች በመውጣታቸው በአንዲት ቤተክርስቲያን ሁለት ፓትርያርክና ሁለት አመራር ሊኖር አይገባም የተለያዩት አባቶች አንድ እስኪሆኑና አንድ አመራር እስኪሆን ድረስ ቤተክርስቲያኗ በገለልተኝነት አቋማ እንድትቀጥል ሆኗል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ይህ የመለያየት መንስዔ ሳይፈታና ምንም ዓይነት ለውጥ ሳያሳይ ከተስፋ መቁረጥና ከእምነት ጽናት ማነስ በመነጨ ይህን የገለልተኝነት አቋም ለመቀየርና ኢትዮጵያ ካሉት አባቶች/ሲኖዶስ ጋር የመቀላቀል ጥያቄ በሰንበት ት/ቤት በቀረበ። በጥያቄውም መነሻነት ጁን 2 ቀን 2013 ዓ.ም በተደረገው የአባላት ጠቅላላ ጉባዔ አብዛኛው የቤተክርስቲያኗ አባላት ቤተክርስቲያናችን ባለችበት አቋሟ እንድትቀጥል የሚፈልጉ መሆናቸውን ባቀረቧቸው አስተያየቶችና የውሳኔ ሐሳብ ቢገልጹም በቤተክርስቲያኗ ተቀዳሚ ካሕን ውግዘት መስይ ቃል ውሳኔ ሳይሰጥ ጉዳዩ በይደር ተይዞ የበለጠ ግንዛቤ እንዲኖር በሚል በፓናል ውይይት እንዲቀርብ ተደረገ። ዲሴምበር 15 ቀን 2013 ዓ.ም በተደረገው የፓናል ውይይት ላይ ባለንበት እንቆይ በሚለው እና ኢትዮጵያ ባለው ሲኖዶስ እንተዳደር በሚለው ሃሳብ የተዘጋጁት ቡድኖች ከጉዳዩ ጋር ይገናኛል ብለው ያመኑበትን ጥናት በጽሑፍ ካቀረቡና ለተለያዩ
ጥያቄዎችም ማብራሪያዎች ከተሰጡ በኋላ( ለ6 ሰዓት የቆየ ስብሰባ ነበር) አባላት ድምጽ እንዲሰጡበት ተደርጎ በስብሰባው ተካፋይ ከሆኑት አባላት ከፈተኛ ቁጥር ያላቸው ቤተክርስቲያኗ ባለችበት የአስተዳደር ገለልተኝነት አቋም እንድትቀጥል ወስነዋል።

ይህንንም ውሳኔ ተከትሎ በተደረጉ የአስተዳደር ቦርድ ስብሰባዎች ላይ አንዳንድ የአስተዳደር ቦርድ አባላት በወቅቱ የስብሰባው ምልዐተ ጉባዔ/ኮረም/ ስላልሞላ ውሳኔውን አንቀበልም በማለታቸውና በተቃራኒው ደግሞ የአስተዳደር ሊቀመንበሩና ሌሎች የቦርድ አባላት የኅዝብን ውሳኔ ማክበር ይገባናል ውሳኔን የመሻር መብት ያለው ጠቅላላ ጉባዔ ብቻ ነው ሲሉ የተለያየ አቋም በመያዛቸው በአስተዳደር ቦርዱ አባላት መካከል በተፈጠረው አለመግባባት ሊቀመንበሩ ጉዳዩን ባለቤቱ ኅዝቡ ተመልክቶ ውሳኔ እንዲሰጥበት አጠቃላይ የስብሰባ ጥሪ ለፌብረዋሪ 16 2014 ጠሩ። ነግር ግን የኅዝቡን ውሳኔ መቀበል ያልፈለጉት የአስተዳደር ቦርድ አባላቱ ጄንዋሪ 23 2014 ባደረጉት ህገወጥ ስብሰባ ሊቀመንበሩን ከሥልጣናቸው አውርደናል ሲሉ ተናገሩ። መጀምሪያ ግን ይህ ሊቀመንበሩ ከሥልጣናቸው ወርደዋል የሚለው ትእዛዝ የመጣው ‘የቤተክርስቲያኑ ጠብቃ ነኝ’ ከምትል አንዲት የሕግ ባለሙያ ሴት ነው። ለዚህች ሴት ማን ቤተክርስቲያኑን እንድትወክል ውል እንደፈረመላት ባይታወቅም የተቀጠረችው በግለሰቦችና በአንዳንድ የቦርድ አባላት እንደሆነ ይነገራል። በቤተክርስቲያናችን መተዳደሪያ ደንብ መሰረት ቤተክርስቲያኑን ወክሎ ማናቸውንም ሰነድ የሚፈርመው ሊቀመንበሩ ብቻ እንደሆነ በአንቀጽ 6 ክፍል 3 ‘ሀ’ 7) ላይ ተደንግጓል። እዚህ ላይ ልብ ሊሉት የሚገባው ነገር ሊቀመንበሩን አውርደናል ባሉበትና ሌላም ባልተሾመበት ሁኔታ ማን በቤተክርስቲያኑ ስም ውል እንደፈረመ ነው። አሁንም ይህ ጠበቃ ለቤተክርስቲያኑ ቀጥረናል ተብሎ የተላለፈው መልእክት ግልጽ አይደለም።

ሊቀመንበሩን ከሥልጣናቸው ለጊዜው አግዶ ለጠቅላላ ጉባዔ ማቅረብ የሚቻልበት የውስጥ አሰራር እያለ ለምን ጠበቃ መቅጠርና ከፍተኛ ወጪ ማስክተል አስፈለገ? ይህ አላስፈላጊ አካሔድ ያሳሰባችው የቦርድ አባላት ሊከተል የሚችለውን ከፍተኛ ወጪ ለማስቆምና የቤተክርስቲያኑን ገንዘብ ለማስጠበቅ ሲሉ የእገዳ ይጣልልን አቤቱታ ለፍርድ ቤት አቅርበዋል።

ስለሆነም እነኝህ ያለአግባብ እየሔዱ ያሉ የቦርድ አባላት የቤተክርስቲያናችንን ሊቀመንበር አውርደናል ካሉ በኋላ የቤተክርስቲያኑን ንብረትና ገንዘብ ለመጠበቅ ሲባል እንዲሁም እየተከሉት ያለውን ከመተዳደሪያ ደንቡና ከስቴቱ የቤተክርስቲያናት ሕግ ወጪ የሆነ አካሔድ ለማስቆም ሲባል ከፍርድ ቤት አስቸኳይ የእገዳ ማዘዣ ለማውጣት የተወሰደውን ርምጃ ነው ቤተክርስቲያኑ ተከሷል በማለት ሕዝቡን ለማደናገር እሞከሩ ያሉት። እውነታው ግን ሕዝቡ ተሰብስቦ በተከሰተው ጉዳይ ላይ ተነጋግሮ ውሳኔ እንዳይሰጥ እንቅፋት የሆኑት እነኝሁ የሕዝቡን ውሳኔ አንቀበልም በማለት ቤተክርስቲያናችንን አሳልፈው ለመስጠት ሁሉንም ሕገ-ወጥ አሰራር እየገፉበት ያሉት የቦርድ አባላት ናቸው። ከጄነዋሪ 11/ 2014 የአስተዳደር ቦርድ ስብሰባ በኋላ ምንም አይነት የአስተዳደር ቦርድ ስብሰባ ተደርጎ አያውቅም። በዚህ ሁኔታ ቤተክርስቲያኑ ተከሷል ጠበቃ ገዝተናል እንዴት ሊባል እንደተቻለም ግራ የሚያጋባ ነው።
ከአራት መቶ በላይ የሚሆን ህዝብ ፔትሺን ፈርሞ አጠቃላይ የአባላት ስብሰባ እንዲደረግ ቢጠይቅም በተጨማሪም ፍርድ ቤቱ ፌብረዋሪ 5 2014 ጉዳያችሁን በጠቅላላ ስብሰባ ፍቱትና አስታውቁኝ በማልት ማሳሰቢያ ቢሰጥም አሻፈረኝ በማለት ያለሕዝቡ ፈቃድና እውቅና ጠበቃ በመቅጠር ከፍተኛ ወጪ ስለተጠየቀ ይህንንም ከፍተኛ ወጪ ከቤተክርስቲያኑ አካውንት የሚያውጡበት አሰራርና ሕግም ስለሌለ ሕዝቡን ‘ቤተክርስቲያናችን ተከሰሰ’ በማለት ከእውነታው የራቀ ውዥንብር አሰራጭተዋል። ለመሆኑ ቤተክርስቲያኑ በምን ጉዳይ ላይ ነው የተከሰሰው??? በወንጄል ነው በፍታብሔር ??? ቤተክርስቲያኑ ማንን ምን ስላደረገ ነው የተከሰሰው ??? ማነውስ የራሱን ቤተክርስቲያን የሚከሰው ???

ከላይ እንደተጠቀሰው የሕዝቡን ውሳኔ አንቀበልም ያሉ የቦርድ አባላት በቤተክርስቲያኑ ገንዘብ ላይ ብክነት እንዳያስከትሉና ያለሕዝቡ ፈቃድ ወደ ኢትዮጵያው ሲኖዶስ ተቀላቅሏል እንዳይሉ የእገዳ ማእቀብ ይደረግን የሚል ጥያቄ ብቻ ነው ለፍርድ ቤት የቀረበው። ይህም ጥያቄ የአራት የቦርድ አባላት ብቻ ሳይሆን ከአራት መቶ በላይ የሆኑ አባላት ፔትሺን የፈረሙበት ጉዳይ ነው። አሁንም በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሕዝቡ ባስቸኳይ ተሰብስቦ በቦርዱ አባላትም ሆነ በማንኛውም ጉዳይ ላይ ውሳኔውን እንዲያሳልፍ የሽምግልና ሒደት/mediation/ እየተከናወነ ሲሆን አሉ የሚባሉ ጉዳዮችን ሁሉ ለሕዝቡ በጠቅላላ ጉባዔ ላይ መግለጽ እየተቻለ ሕዝብን ለማሸበርና ያልተደረገውን ተደርጓል ተብሎ የተላለፈው መልእክት ውሸት መሆኑን ሁሉም እንዲያውቀው እንወዳለን።

በመጨረሻም የሁሉም ጉዳይ ባለቤትና የመጨረሻ ውሳኔ ሰጪ የአባላት ጠቅላላ ጉባዔ ስለሆነ የአባላት ጠቅላላ ጉባዔ በቀረቡት ፔትሺኖች መሠረት ባስቸኳይ እንዲጠራ እናሳስባለን።

መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያናችንን በሰላምና በአንድነቷ ያጽናልን። አሜን!

Ze-Habesha Website may contain advice, opinions, and statements of various information and content providers. The Website neither represents nor endorses the accuracy of information or endorses the contents provided by external sources. All blog posts and comments are the opinion of the authors.

Print Friendly

Source Article from http://www.zehabesha.com/amharic/archives/13687

You might like

About the Author: AddisZena

Leave a Reply