Ethiopia Ethiopian News

መንበረ ጵጵስናውን እንግሊዝ ሀገር ለንደን ከተማ ያደረገው የሰሜን ምዕራብ አውሮፓ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት በሎንደን ከተማ ነዋሪ የሆኑትን «ቄስ» ብርሃኑ ብሥራትን ከሥልጣነ ክህነት አገልሎት መሻራቸውን አስታወቀ፤

 

«ቄስ» ብርሃኑ ብሥራትን

«ቄስ» ብርሃኑ ብሥራት

የዛሬ አርባ ዓመት ገደማ በአውሮፓ ለመጀመሪያ ጌዜ በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ፣ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳ ዘኢትዮጵያ መልካም ፈቃድ በአባ አረጋዊ ወልደ ገብርኤል(ቆሞስ) በኋላ ብፁዕ አቡነ ዮሐን አስተዳዳሪነት ለረጅም ጊዜ መንፈሳዊ አገልግሎት ስትሰጥ በቆየችውና ቀጥሎም በእንግሊዝ ሀገር እና በመላው ዓለም በሚገኙ የጽዮን ወዳጆጅ ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች የዘወትር ጸሎት፣  የጉልበትና የገንዘብ አስተጽዖ በአንድ ሚሊዮን ሰባት መቶ ሺህ የእንግሊዝ ገንዘብ በለንደን ከተማ ማዕከላዊ በሆነ ቦታ የራስዋ የሆነ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ገዝታ ለሕዝበ ክርስቲያኑ የተሟላ አገልግሎት በመስጠት ላይ ትገናለች። ይሁን እንጂ የሕንጻው ክፍያ ከተጠናቀቀ በኋላ ጥቂት ግለሰቦች ቤተ ክርስቲያኑን ከቅዱስ ሲኖዶስ ማዕከላዊ አስተዳደር፣ ከቃለ ዓዋዲው መመሪያና ትዕዛዝ አስወጥተው በግለሰብ አደረጃጀት ሕንጻውን በግል ይዞታ ለመቆጣጠር ባወጡት የተሳሳተ ዕቅድና ዓላማ ምክንያት ችግር ተፈጥሮ መንፈሳዊ አገልግሎቱ በግፍ ተቋርጦ ቤተ ክርስቲያኑ ከዘጠኝ ወራት በላይ አላግባብ ተዘግቶ ካህናትና ምዕመናንን በከፍተኛ ደረጃ ሲያዛዝናቸውና ሲያስለቅሳቸው ቆይቷል።

 

በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ የተፈጠረው መንፈሳዊና ክርስቲያናዊ መንገድ ያልተከተለ፣ ከመጠን ያለፈና መረን የለቀቀ ረብሻ እጅግ በጣም በሚያሳዝን ሁኔታ በአብዛኛው በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ተዘግቦ በዓለም ላይ ያሉትን የቤተ ክርስቲይናችን ተከታዮች ሁሉ ያሳዘነ፣ በስደት የሚገኘውን የማኅበረሰባችን ገጽታ ያበላሸ አሳዛኝ ታሪክ ሆኖ የተዘገበ ተግባር ሲሆን፤ ቄስ ብርሃኑ ብሥራት የዚህ  ሕገ ቤተ ክርስቲያን የጣሰ፣ በቃለ ዓዋዲ የማይመራ የአመጽ ቡድን አስተባባሪና መሪ በመሆን  ለችግሩ ሁሉ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያደረጉና እያደረጉ የሚገኙ አርዓያነት የጎደላቸው ግለሰብ መሆናቸውን ካህናትና ምእመናን ሲያሳውቁ ቆይተዋል።

 

ቀደም ሲል የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ  ትዕዛዝ ብፁዕ አቡነ ገብርኤል እና ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ ወደ እንግሊዝ ሀገር ተልከው ከሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ እንጦንስ ጋር በመሆን ለችግሩ መፈትሄ ለመስጠት ከአንድ ወር በላይ ከፍተኛ ሙከራ ያደረጉ ቢሆንም ሊሳካ አልቻለም። ከአንድ ወር በላይ ለፈጀው የሰላም ጥረት አለመሳካት ምክንያቱ በ«ቄስ» ብርሃኑ ብሥራት እንመራለን የሚሉ ግለሰቦች ደንብ በማርቀቅ ስም «ፕሮቴስታንታዊ» ዓላማና አወቃቀር ያለው «መተዳደሪያ ደንብ» አርቅቀው ቤተ ክርስቲያኑን ለረጅም ጊዜ ተመዝግቦበት ከቆየው የቤተ ክርስቲያኗን ሃይማኖታዊ ልዕልና የማይጋፋ፣ ሕጋዊ የንብረትና ፋይናንስ ቁጥጥር ያለው የእንግሊዝ ሀገር የምግባረ ሰናይ (Charitable Trust) ምዝገባ  አስወጥተው፤ ኃላፊነቱ በተወሰነ የግል ኩባንያ (Private Company Limited by Guarantee) አስመዝግበው ሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑን ለመቆጣጠርና የሚፈልጉትን ሁሉ ለማድረግ በቡደን ተደራጅተው ያወጡትን ዕቅድ መመሪያ አድርገው የሚንቀሳቀሱ በመሆናቸው እንደሆነ ተገልጿል። በዚህ ምክንያት ብጹዓን ሊቃለ ጳጳሳቱ በትዕግሥት የተቻላቸውን ያህል ቢሞክሩም ግለሰቦቹን ከስህተታቸው አስተምሮና አርሞ ወደ ሕገ ቤተ ክርስቲያን ለመመለስና የተፈጠረውን ችግር በመንፈሳዊ አስተዳደራዊ ዳኝነት ለመፍታት ካለመቻላቸውም በላይ፤ «ቄስ» ብርሃኑ ብሥራት የዚህ ሁሉ የተሳሳተና ከሕገ ቤተ ክርስቲያን የወጣ መንገድ ጠራጊ በመሆን፤ ሊቃነ ጳጳሳቱ የሰጡትን መንፈሳዊ መመሪያ ተግባራዊ ለማድረግ ፈቃደኛ አለመሆናቸው  ችግሩን ይበልጥ እንዳባባሰው ተገልጧል።

 

ብጹዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ የተዘጋውን ቤተ ክርስቲያን ከፍተው በሐዘንና በልቅሶ ላይ ላሉት ምዕመናን መንፈሳዊ አገልግሎት ለመስጠት ሙከራ ቢያደርጉም፤ እነዚሁ ወገኖች የሌሎች እምነት ተከታዮችንና የፓለቲካ ቅራኔ አለን ብለው የተደራጁትን ሁሉ በማስተባበር በቤተ ክርስቲያኑ ግቢ ውስጥ ቅጥ ያጣ የረብሻና የሁከት ሰልፍ በማድረግ ቤተ ክርስቲያኑን እንዳይከፈት እጅግ በጣም አስቸጋሪና አሳዛኝ የሆነ ተግባር ሲፈጽሙ መቆየታቸው ተገልጿል።

 

ለሁለተኛ ጊዜ ሊቀ ጳጳሱ አቡነ እንጦንስ ነሐሴ 25 ቀን 2005 ዓ.ም (25/8/2013) ግራ ቀኙን ጎራ ለይተው በተሰበሰቡበት በቤተ ክርስቲያኑ ግቢ ውስጥ ተገኝተው «የተፈጠረውን ችግር በጠጴዛ ዙሪያ በሕገ ቤተ ክርስቲያን ይፈታ፣ ቤተ ክርስቲያኑ ያለምንም ቅደመ ሁኔታ ተከፍቶ መንፈሳዊ አገልግሎት ይከናወንበት» በማለት መንፈሳዊ መመሪያ ቢሰጡም ግለሰቦች ቤተ ክርስቲያንኑ እንዳይከፈት አመጻቸውን አጠናክረው  ሲያካሂዱ እንደነበረ በወቅቱ በመገናኛ ብዙኃን የተዘገበውን ማስረጃ በማድረግ ማብራሪያ ተሰጥቷል።

 

በመቀጠልም ብፁዕ አቡነ ገብርኤልና ብፁዕ አቡነ ያዕቆብ ከሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ጋር በመሆን ለሦስተኛ ጊዜ ቤተ ክርስቲያኑን ከፍቶ አገልግሎት ለመስጠት ከፍተኛ ሙከራ ቢያደርጉም አሁንም የቤተ ክርስቲያኑን ሕንጻ በግል ባለቤትነትና ይዞታ ለመቀማት የተነሱት የቄስ ብርሃኑ ተከታዮች በፈጠሩት ኢ-ክርስቲያናዊ አመጽ ምክንያት ቤተ ክርስቲያኑን መክፈት ሳይቻል እንደቀረ ታውቋል።

በወቅቱ ቤተ ክርስቲያኑ እንዳይከፈት ለማደረግ የተደረገውን አመጽ፣ በሊቃነ ጳጳሳቱ ላይ የውረደውን የስድብ ውርጅብኝ፣ ባጠቃላይ ሁከቱንና እረብሻውን በቦታው ላይ ተገኝተው የተመለከቱት የደቡብ አፍሪካ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ያዕቆብ «በቤተ ክርስቲያን ሕይወቴ ክርስቲያን ቤተ ክርስቲያን ለጸሎትና ለቅዳሴ እንዳይከፈት ሲያውክ፣ ሰይጣን ሥጋ ለብሶ ሲንቀሳቀስ ያየሁበት ወቅት ቢኖር ይህ ነው» በማለት በጥልቅ ሀዘን ገልጸውታል።

 

የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ባለባቸው መንፈሳዊ ኃላፊነት ቄስ ብርሃኑ ብሥራትን በአካል አነጋግሮ መመሪያና ምክር ለመስጠት በተደጋጋሚ ሙከራ ቢያደርጉም፤ ቄሱ ግለስቦቹ በቤተ ክርስቲያን ላይ የሚያሳዩትን ፍጹም ሕገ ወጥ አመጽ እንደ ትልቅ ደጀን በመቁጠር ለመንፈሳዊ ጥሪው በጎ ምላሽ እንዳልሰጡ ታውቋል። ካህናትንም በሽምግልና መኖሪያ ቤታቸው ድረስ በመላክ የሚሄዱበት መንገድ ሁሉ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን የጣሰ መሆኑን በመግለጽ የእናት ቤተ ክርስቲያንን ማከላዊ አስተዳደር ጠብቆ ወደማስጠበቁ በጎ ጎዳና እንዲመለሱ ቢጠየቁም ሊመለሱ እንዳልቻሉ ተብራርቷል።

 

ከዚያም አስቀደሞ ሰኔ 7 ቀን 2005ዓ.ም፣ ሐምሌ 24 ቀን 2005 ዓ.ም አንዲሁም ነሐሴ 15 ቀን 2005 ዓ.ም በተጻፈ ደብዳቤ ሊቀ ጳጳሱ ምክርና መመሪያ ለመስጠት ቢጠሯቸው ጥሪውን አክብረው ለመገኘት ፈቃደኛ አለመሆናቸው ተገልጧል። በጠቅላላው «ቄስ» ብርሃኑ ብሥራት ክህነቱን በመንፈሳዊ አደራነት ለሰጠቻቸው ቅድስት ቤተ ከርስቲያን ሕግጋትና ቀኖና ከመታዘዝ ይልቅ ግለሶቦቹን ስቶ በማሳት ከዛም አልፎ እነሱን በአዳራሽ በመሰብሰብ እራሳቸውን በራሳቸው በሕገ ወጥ መንገድ የቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ አድርገው በመሾም፤ በሕዝብ የተመረጠውን ሰበካ ጉባዔ የቤተ ክርስቲያን ቁልፍ፣ ሀብትና ንብረት አስረክቡኝ የሚልና የሚያስገድድ ደብዳቤ መጻፋቸው የገለሰቡን ሕግ የመተላለፍ ተግባርና ከቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ቁጥጥር ውጭ የሆኑ መሆኑን እንደሚያስረዳ በስፋት ተብራርቷል።

 

በሰሜን ምዕራብ አውሮፓ ሀገረ ስብከት መመሪያ፣ በደብሩ ሰበካ አስተዳደር ጉባኤ ያላሰለሰ ጥረት፣ “አቅሌስያ” በሚል ስም በተደራጁ ካህናት፣ ምዕመናንና የሰንበት ት/ቤት አባላት ድጋፍ፣ ከሕግ አማካሪ በተገኘ ብስለት የተሞላበት የሕግ ምክር፣ በአካባቢው ፖሊስና ጸጥታ ኃይሎች ቀና ትብብር ታህሳስ 20 ቀን 2006 ዓ.ም የእመቤተችን ቅድስት ድንግል ማርያም መታሰቢያ ውርኀዊ በዓል ዋዜማ ዕለት ቁጥራቸው ብዙ የሆነ ሕዝበ ክርስቲያን በተገኙበት ከዘጠኝ ወራት በላይ ከቄስ ብርሃኑ ብሥራት ጋር የጠበቀ ግንኙነት ያላቸው እነዚሁ ወገኖች ባስነሱት ኢ-ክርስቲያናዊ አመጽ ምክንያት በግፍ የተዘጋው ቤተ ክርስቲያን በብጹዕ ሊቀ ጳጳስ አቡነ እንጦንስ ቡራኬ ተከፍቶ በአራቱም ማዕዘን ወንጌል እየተነበበ ቅዳሴ ቤቱ ቀኖና ቤተ ክርስቲያን በሚያዘው መሠረት ተከፍቶ መንፈሳዊ አገልግሎቱን በይፋ እየተከናወነበት  መሆኑን የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት አስታውቋል።

 

ቀጥሎም  በዘመነ አስተርዕዮ የሚከበሩት ዓበይት በዓላት የጌታችንና መደንኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የልደት፣ የጥምቀትና የእመቤታችን በዓላት ሁሉ በሊቀ ጳጳሱ መሪነት በብዙ ሺህ የሚቆጠር ምዕመናን በተገኙበት በለንደን ደብረ ጽዮን ቅደስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ታላቅ ድምቀትና አንድነት ተከብሯል። በተለይም የጥምቀቱ በዓል በለንደን ከተማ የሚገኙ አድባራት ታቦታት፣ ካህናት፣ ምእመናን እና የሰንበት ት/ቤት መዘምራን በአንድነት ሆነው “ጃንሜዳ በለንደን” የተባለለት ታላቅ የአንድነት በዓል የተከበረ መሆኑ ተዘግቧል። ይህ ሁሉ ሲሆን «ቄስ» ብርሃኑ ብሥራት  የቤተ ክርስቲያኑን ሕንጻ በኃይል ቀምተው በግለሰብ ይዞታ በገለልተኝነትና በግል ባለቤትነት ለመቆጣጠር የሚጓዙትን በማሳመጽ በግቢው ውስጥ ድንኳን በመጣል «በእኛ እምነት ቤተ ክርስቲያኑ አልተከፈተም» በማለት ሊቀ ጳጳሱ ከመሚመሩት ጉባዔ ከፍለው ከመሠረታዊው ኦርቶዶክሳዊ የሥርዓተ ሃይመኖት አፈጻጻም ተለይተው መዋላቸው ተረጋግጧል።

 

ቄስ ብርሃኑ ብሥራት በርዕሰ አድባራት ሎንደን ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳሱ ሥርዓተ ቅዳሴ እየመሩ ባለበት፣ መንፈሳዊ ትምህርት፣ ቃለ ምዕዳንና ጽሎተ ቡራኬ በሚሰጡበት ተመሳሳይ ሰዓት፤ ግለስቦችን ወደ ቤተ ክርስቲያን እንዳይገቡ በመከልከል በተመሳሳይ ጊዜ ሁለተኛ ተአምረ ማርያም፣ ሁለተኛ ኪዳን፣ ሁለተኛ ወንጌል፣ ሁለተኛ ሥርዓተ ቅዳሴ እያደረጉ፣ ቤተ መቅደስ ገብቶ ያልተባረከ ማዕጠንት እያጠኑ በቤተ ክርስቲያን የአንድነት መንፈሳዊ አገልግሎት በአንዲት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እጅግ በጣም ታይቶ የማይታወቅ መንፈሳዊነት የጎደለው፣ ክህነታዊ አርዓያነትና ኃላፊነት የተለየው ተግባር ሲፈጽሙ መቆየታቸው በስፋት ተብራርቷል።

 

ቄስ ብርሃኑ ብሥራት ከ1986 ዓ/ም ጀምሮ በብጹዕ አቡነ ዮሐንስ አሳሳቢነት፤ በብጹዕ ወዱስ አቡነ ጳውሎስ መልካም ፈቃድ ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት በጀት ተፈቅዶ በወቅቱ በአዲስ አበባ ከተማ ይኖሩ ለነበሩት ባለቤታቸውና ቤተ ሰቦቻቸው ጊዜው ይፈቅድ በነበረው መሠረት በወር ብር 500(አምስት መቶ ብር) ይከፈላቸው እንደነበር፣ እስከ ቅርብ ጊዜ ደረስ በርዕሰ አድባራት ለንደን ደብረ ጽዮን አራት እሁድ ብቻ ቀድሰው በየወሩ ከአንድ ሺህ አንድ መቶ ሰማንያ ሁለት የእንግሊዝ ገንዘብ  ቋሚና መደበኛ ክፍያ ይከፈላቸው እንደነበር ታውቋል። ነገር ግን ቄሱ ቤተ ክርስቲያኗ ከቅዱስ ሲኖዶስ ማዕከላዊ አስተዳደርና ከሀገረ ስብከት አመራር ተለይታ ገለልተኛ ሆና እሳቸው ብቻ ተጠቃሚ ለመሆን ባላቸው የተሳሳተ ዓላማ ምክንያት፤ ከአሁን በፊት ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ለሐዋርያዊ ተልዕኮ ወደ እንግሊዝ ሀገር ተልከው በሚመጡ አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ላይ አድማና አመጽ በማስነሳት መንፈሳዊ ተልዕኳቸውን በአግባቡ እንዳይወጡ እንቅፋት ሲፈጥሩና ስቶ የማሳት ተገባር ሲፈጽሙ እንደቆዮ ስለመሆናቸው በሕይወተ ሥጋ ካሉት መካከል ብፁዕ አቡነ አትናቴዎስ፣ ብፁዕ አቡነ አረጋዊ፣ ብጹዕ አቡነ ገብርኤል፣ ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ፣ ብጹዕ አቡነ ኢሳይያስ፣ ሊቀ ካህናት ብርሃኑ ገብረ አማኑኤል፣ ንቡረ ዕድ አባ ወልደ ማርቆስ፣ እና ሌሎችም  በአስረጂነት ሊጠቀሱ የሚችሉ መሆኑን ተገልጧል።

 

በመጨረሻም ቄስ ብርሃኑ ብሥራት ግየሚመሯቸው ግለሰቦች በተከራዩላቸው ጠበቃቸው አማካኝነት ብፁዕ አቡነ እንጦንስ ሊቀ ጳጳስ ወደ ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን መጥተው መንፈሳዊ አገልግሎት እንዳይሰጡና በቤተ ክርስቲያኑ ግቢ ውስጥ እንዳይታዩ ለማድረግ የፍርድ ቤት ዕገዳ ለማውጣጥ ከፍተኛ ኢ-ክርስቲያናዊ የሆነ ሙከራ እንዳደረጉ የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት አታውቋል ።

 

የሀገረ ስበከቱ ሊቀ ጳጳስ አቡነ እንጦንስ ባለባቸው ኃላፊነት ቄስ ብርሃኑ ብሥራትን መክሮ፣ አስተምሮና ገስጾ  ወደ ሕገ ቤተ ክርስቲያን ለመመለስ የተቻላቸውን ሁሉ በማድረግ ሰፊ ጊዜ የወሰደ ተደጋጋሚ ሙከራ ቢያደርጉም ሊመለሱ ባለማቻላቸው የተሰማቸውን ከፈተኛ ሐዘን ገልጸው ከጸለዩ በኃላ የሚከተለውን ውሳኔ እንዳስተላለፉ ተዘግቧል።

 

ከዚህ ሁሉ ጥረት በኋላ ከመጽሐፍ ቅዱስ “ንግራ ለቤተ ክርስትያን” (ማቴ፤ 18፡18) የሚለውን፣ ቀኖና ሐዋርያት አንቀጽ 39፣ ከቃለ ዓዋዲ አንቀጽ 63፤ ቁጥር 2 እና 3 ያሉትን ኃይለ ቃላት በማገናዘብ፤ ይልቁንም ፍትሕ መንፈሳዊ «ካህኑ ኤጴስ ቆጶሱን አልታዘዘው ቢል (ቢንቀው)፣ ብቻውን ቤተ መቅደስ ቢሠራ፤ ኤጴስ ቆጶሱም ሦስት ጊዜ ቢጠራው ትዕዛዙን ተቀብሎ መልስ ባይሰጥ፣ እሱ ከማዕረገ ክህነቱ ይሻር፤ ተከታዮቹም ይሻሩ።» (ፍመ. ምዕራፍ 6፤ አንቀጽ 228፤ 3ኛረስጠብ 22) በማለት የደነገገውን ዋቢ በማደረግ “ቄስ” ብርሃኑ ብሥራት በየትኛውም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ አድባራትና ገዳማት ሁሉ በቅስና የሥልጣነ ክህነት መንፈሳዊ አገልግሉት አንዳይሰጡ ከሥልጣነ ክነታቸው የተሻሩ መሆኑን ገልጸዋል።

 

ብጹዕ ሊቀ ጳጳሱ የጻፉት ደብዳቤ እንደሚያስረዳው ከእንግዲህ “ቄስ” ብርሃኑ ብሥራት እንደተለመደው በማን አለብኝነትና በዕብሪት በስልጣነ ክህነት የሚሰጡት ማንኛውም መንፈሳዊ አገልግሉት በሐዋርያት ትዛዝ “ዘአሰርክሙ በምድር ይኩን እሱረ በሰማያት፤ ወዘፈታሕክሙ በምድር ይኩን ፍቱሐ በሰማያት” መሠረት ሀብተ መንፈስ ቅዱስ የማያሰጥ ሀብተ ስርየት የተለየው የታሰረና የተሻረ መሆኑን አብራርተው፤ “ቄስ” ብርሃኑ ብሥራት ይህን መንፈሳዊ ዳኝነትና ውሳኔ ተቀብለው ተግባራዊ ባያደርጉና በመንፈስ ቅዱስ ሥልጣን ላይ ቢያምጹ በውግዘት ከማኅበረ ቤተ ክርስቲያን ሊለዩ እንደሚችሉ አስጠንቅቀዋል።

 

በመጨረሻም የሰሜን ምዕራብ አውሮፓ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ወደፊት በዚህ ዓይነት የኢትዮጵያ አርቶዶክስ ተዋሕዶ ሕገ ቤተ ክርስቲያንን የሚያፈርስ፤ በቤተ ክርስቲያን ማዕከላዊ አስተዳደር በአመጽ ክንዱን የሚያነሳ፣ በጠቅላላው ከአንዲት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአምልኮት አፈጻጸም ሥርዓት እና ቀኖና እንዲሁም ከቃለ አዋዲው መንፈሳዊ የአንድነት መመሪያ ውጭ ሆኖ ለመንቀሳቀስ የሚሞክር ወይም እንዲህ ያለውን ሕገ ወጥ ተግባር የሚያበረታታ፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተባባሪ የሚሆን አገልጋይ ካህን ቢኖርና በበቂ ማስረጃ ከተረጋገጠበት ቤተ ክርስቲያን ልትታገሰው የማትችል መሆኑን በጥብቅ አሳስበዋል።

 

የ“ቄስ” ብርሃኑ ብሥራት ሥልጣነ ክህነት የተሻረበትን ሕጋዊ ደብዳቤ ሙሉ ቃል ከዚህ ቀጥሎ ይመልከቱ።

 

Download (PDF, 1021KB)

 

Ze-Habesha Website may contain advice, opinions, and statements of various information and content providers. The Website neither represents nor endorses the accuracy of information or endorses the contents provided by external sources. All blog posts and comments are the opinion of the authors.

Print Friendly

Source Article from https://www.zehabesha.com/amharic/archives/13919

Post Comment