Ethiopia Ethiopian News

የጠፋውን የማሌዥያ አውሮፕላን የበላው ጅብ አልጮህ አለ፤ (ከዚህ በፊት 5 አውሮፕላኖች ጠፍተው እንደነበር ያውቁ ኖሯል?)

ከአትላንታው አድማስ ራድዮ

ስለ ማሌዢያው የበረራ ቁጥር 370፣ የተሰወረ አውሮፕላን መዘገብ እጅግ ከባድ ነው። ምክንያቱም ነገሮች በየደቂቃው ይቀያየራሉና። ገና ሲጀመር፣ አውሮፕላኑ ለመጨረሻው ጊዜ ድምጽ ያሰማበት ሰአት ልክ አልነበረም፣ ከዚያ ቀጥሎ ሁለት ጥቁሮች በሃሰት ፓስፖርት ተሳፍረዋል ተባለ፣ ጥቂት ቆይቶ ጥቁር አይደሉም፣ ኢራናውያን ናቸው ተባለ፣ .. ከዚያ በኋላ 6 ሰዎች አውሮፕላኑ ውስጥ ሊገቡ ካሉ በኋላ ሃሳባቸውን ቀይረዋል ተባለ፣ ጥቂት ቆይቶ ስድስት አይደሉም 2 ናቸው፣ እነሱም ገና ከቤታቸው ሳይወጡ ሃሳባቸውን የቀየሩ ናቸው ተባለ ….፣ ከዚያ ደግሞ አውሮፕላኑ ከጠፋ ከ 48 ሰአት በኋላ የአንዳንድ ተሳፋሪዎች ስልክ ይጠራል ተባለ . ጥቂት ቆይቶ ፣ ውሸት ነው የማንም ስልክ አይጠራም ተብሎ ተነገረ …፣ ከዚያ በኋላ ቻይናዎች በአንድ የቻይና ባህር ላይ የአውሮፕላኑ ስባሪን አይተናል አሉ ተባለ ..፣ ጥቂት ቆይቶ ውሸት ነው አላዩም በሚል ተስተባበበለ።
Malaysia-Airlines
እያንዳንዱ የሚነገር ጉዳይ ልብ የሚያንጠለጥል ቢሆንም፣ በዚህ በዓለማችን የበረራ ታሪክ እጅግ ውስብስብና አሰገራሚ የሆነ መሰወር ጉዳይ ሁሉም መላምቱን ለመስጠት ቢቸኩል የሚፈርድ አልነበረም። እንደተባለው አውሮፕላኑ በቴክኒክ ችግር አይደለም ድምጹን ያጠፋው፣ እንደተባለው ካቅሙ በላይ የሆነ ነገር ገጥሞትም አይደለም።

ምናልባት ያለፉትን ሰባት ቀናት የተለያዩ ነገሮችን ሰምታችሁ ይሆናልና ቀጥታ ወደፊት በመፈናጠር ዛሬ ጉዳዩ ከደረሰበት ነገር እንጅምር። ከዚያ በኋላ ከዚህ በፊት የጠፉ አውሮፕላኖችን ታሪክ እናሳያችኋለን።

ዛሬ ጠዋት የማሌዥያ ጠቅላይ ሚኒስትርና የአየር ሃይል ሃላፊያቸው ያሉበትን ደረጃ ለመናገር ብቅ ብለው ነበር። በነሱ መረጃ መሰረት ዛሬ የተነገረው ትልቁ ነገር አውሮፕላኑ በቴክኒካል ችግር ሳይሆን ሆን ተብሎ ድምጹን ማጥፋቱንና ፣ ምናልባትም የመጨረሻውን ግንኙነት ከተቆጣጣሪዎች ጋር ካደረገ በኋላ ቢያንስ 7 ሰአት ያህል ሳይበር እንዳልቀረ መናገራቸው ነው፡፡ ያ ማለት አውሮፕላኑ ተጠልፏል ወይም ታግቷል። ይህ የሆነው ደግሞ ወይም ከተሳፋሪዎች መካከል በአንዱ ወይም ደግሞ እንደ ኢትዮጵያው አየርመንገድ በራሱ ፓይለት ተጠልፎ ነው ማለት ነው።

ይህ የዛሬው ውጤት እስካሁን አውሮፕላኑ ሲፈለግ የነበረባቸውን ቦታዎች ሁሉ ፉርሽ እንደነበሩ የሚያሳይ ነው። ለመሆኑ አውሮፕላኑ ከምድር ተቆጣጣሪዎች ጋር እንዳይገናኝ፣ ሆን ብሎ መገናኛውን የነቀለው ሰው ማነው? ይህ ሊሆን የሚችለው እንደ አቪየሽን ሃላፊዎች ወይ በራሱ በፓይለቱ ነው፣ ወይም ደግሞ በጣም ጥሩ የሆነ የፓይለትነት ችሎታ ባለው ጠላፊ ነው። ይህ ከሆነ ደግሞ አውሮፕላኑ ቢያንስ ለሰባት ሰአት ያህል በምዕራብ አቅጣጫ ከተጓዘ ሊደርስ የሚችለው ሁለት ቦታ ነው፣ አንዱ አንዳማን ደሴቶች ሲሆን ሁለተኛው ህንድ ውቂያኖስ መካከል ነው። እንደ ማሌዥያ ባለሥልጣኖች ገለጻ አውሮፕላኑ የያዘው ነዳጅ ቢያንስ ሰባት ሰአት ያህል ያስኬደዋል። ያ ማለት ከዚያ በላይ መሄድ ስለማይችል፣ ወይም አንዱ የተደበቀ ደሴት አርፏል፣ ወይም ህንድ ውቂያኖስ መካከል ተከስክሷል። አሁን ያለው መላ ምት ይህ ነው።

ይህም ቢሆን እንቆቅልሹን የሚፈታው አይደለም። ለመሆኑ ከአየር መንገዱ ጋር ከ1981 ዓ.ም ጀምሮ የቆየው ፓይለት፣ የቤተሰብም የሆነ የሌላ ችግር ያልታየበት፣ .. ጥሩ ምግባር እንዳለው የተመሰከረለት፣ በትዳሩ ከ20 ዓመት በላይ የቆየው ፓይለት እንዴት ሆን ብሎ አውሮፕላኑን ይዞ ይሰወራል? ይህ አንዱ ጥያቄ ነው፡ በሌላ በኩል የ 27 ዓመቱ ረዳት ፓይለት አብዱል ሃሚድ፣ ከአየር መንገዱ ጋር ለ7 ዓመት ሰርቷል፣ የተከበረና ምንም አይነት የሚያጠራጥር ነገር የለሌበት ነው። ርግጥ ከዓመታት በፊት ከተሳፋሪዎች መካከል ሁለት ሴቶችን ውስጥ ድረስ ጋብዞና አጠገቡ አስቀምጦ መጓዙ ቢነገርና ይህም የአየር መንገድ ህግን መተላለፍ ቢሆንም፣ በጉርምስና ተሳብቦ ከመቅረቱ በቀር ሌላ እንዲህ ያደርጋል ተብሎ የሚያስገምት ነገር ምንም አልተገኘም።

ከመንገደኞች መካከል ከሆነስ የአውሮፕላን እገታው የተደረገው ማን አደረገው? ለምንስ አደረገው? ያልተፈታ እንቆቅልሽ ነው። ከመንገደኞቹ አብዛኞቹ ቻይኖች እንደመሆናቸው አልቃይዳና ታሊባን በዚህ ድርጊት ይኖራሉ ብሎ ማሰብ ከባድ ነው። ርግጥ አንዳንድ ተንታኞች ከቻይና አንድ ግዛትን ለመገንጠል የሚታገልና ከዚህ በፊት አንድ የቻይና አውሮፕላን ለመጥለፍ የሞከረ አንድ ድርጅት እንዳለ በማስታወስ ይመዝገብልን እያሉ ነው። አስገራሚው ነገር ግን፣ ይህ ከሆነ ጠላፊዎቹ ወይም አጋቾቹ ወይም ድርጊቱ የፈጸመው ማንም ይሁን ማን፣ እንዴት ምክንያቱንና የሚፈልገውን አልተናገረም? እንዲሁ ዝም ብለን እንሙት፣ ድምጻችንን እናጥፋ ብሎ እንዴት ይወስናል? ያልተፈታ እንቆቅልሽ ነው።

ነገር ግን አሁን ባለው የነገሮች ግጥምጥም አውሮፕላኑ የቴክኒክ ብልሽት አልገጠመው ይልቁኑ ሆን ተብሎ ታግቶ ወይም ፓይለቱ ራሱ አግቶት የሆነ ቦታ ወስዶታል ወይም ውቂያኖስ መካከል ከስክሶታል። ይህ ደግሞ በቅርብ ከሆነውና የራስን አውሮፕላን ጠለፈ ከተባለው የኢትዮጵያው ሃይለመድህን ታሪክ ጋር ለማመሳሰል የሞከሩም ነበሩ።

ከዚህ በፊት የጠፉ አውሮፕላኖች ተገኝተዋል? የጠፉስ አሉ?

አዎ አሉ።
– ለምሳሌ በሜይ ወር 2003 ዓ.ም የኡጋንዳ ንብረት የሆነው ቦይንግ 727 ድንገት ሳይፈቀድለት ከአየር ማረፊያው ተነስቶ በመብረር ያልታወቀ ቦታ ሄዷል – እስካሁንም የት እንደገባ አልተገኘም። ፓይለቱና ረዳቱ ብቻ እንጂ ተሳፋሪ አልነበረውም።
– የፈረንሳይ አየር መንገድ በረራ ቁጥር 447 በ2009 ዓ.ም ድንገት ጠፍቶ ፣ ስብርባሪው ህንድ ውቂያኖስ ላይ የተገኘው ከሁለት ሳምንት በኋላ ነበር።
– የትራንስ ዎርልድ አየር መንገድ ንብረት የሆነው አውሮፕላን በበረራ ቁጥር 800 ጉዞ ከጀመረ በኋላ አየር ላይ በመፈንዳቱ 230 ሰዎች አልቀዋል። ይህ የሆነው በ1996 ዓም. ነው።
– የታይገር አየር መንገድ ንብረት የሆነው አውሮፕላን ፣ በበረራ ቁጥር 793 ጉዞ ከጀመረ በኋላ 106 ሰዎችን እንደጫነ የት እንደገባ አልታወቀም ፣ ይህ ይሆነው በ1962 ዓ.ም ቢሆንም፣ ዛሬም ድረስ ምን እንዳጋጠመው የሚያውቅ የለም።
– በ1957 ዓ.ም የፓን አሜሪካ አየር መንገድ አውሮፕላን ቦይንግ 337 44 ሰዎችን እንደጫነ አየር ላይ ጠፋ፣ከአንድ ሳምንት በኋላ ስብርባሪው ውቂያኖስ ላይ ተገኘ።

እነዚህ ሁሉ አስገራሚ ታሪኮች ናቸው። አንዳንዶቹ ምናልባት ቴክኖሎጂ በጣም ባልዳበረበት ወቅት ሊሆኑ ይችላሉ። አሁን 43 መርከቦች፣ 58 አውሮፕላኖች፣ 14 አገሮች ፍለጋውን እያጣደፉ ቢሆንም፣ የመጥፋቱ እንቆቆልሽ ግን ፣ አገር ስጠኝ ብለን የምንፈታው አልሆነም።

Ze-Habesha Website may contain advice, opinions, and statements of various information and content providers. The Website neither represents nor endorses the accuracy of information or endorses the contents provided by external sources. All blog posts and comments are the opinion of the authors.

Print Friendly

Source Article from http://www.zehabesha.com/amharic/archives/13644

Post Comment