Ethiopia Ethiopian News

የዓረና መሪዎች በእንደርታ ኲሓ ከተማ በፖሊስ ታሰሩ

አብርሃ ደስታ ከመቀሌ

Arena-Tigray-logoየዓረና አመራር አባላት የሆኑት አቶ ብርሃኑ በርሀ፣ መምህር የማነ ንጉሰና አቶ ፅጋቡ ቆባዕ በፖሊስ ተደበደቡ፤ በመጨረሻም በኲሓ ከተማ ፖሊስ ታሰሩ። የታሰሩበት ምክንያት ለስብሰባ በማይክሮፎን ቀስቅሳችኋል የሚል ነው። ነገ እሁድ በኲሓ ከተማ ማዘጋጃቤት አዳራሽ ስብሰባ ለማድረግ የተፈቀደልን ሲሆን ቅስቀሳ ለማካሄድ ግን ተከልክለናል። ዛሬ ጧት አቶ ዓምዶም ገብረስላሴና መምህር ዮሃንስ ካሕሳይ ቅስቀሳ ሲያደርጉ በዓይናለም ከተማ ለሰዓታት ታስረው ተለቀዋል። የህወሓት ካድሬዎች ዓረና የማዳበርያ ዕዳ እንደሚሰርዝ፣ መሬት የህዝብ እንደሚያደርግ፣ የሊዝ አዋጅ እንደሚያስቀር ወዘተ በማይክሮፎን እንዳይናገር አስጠንቅቁት ተብለናል ሲሉ የህወሓት ካድሬዎች ራሳቸው አረጋግጠውልናል። አሁን የኲሓ ከተማ ቅስቀሳችን በአባሎቻችን መደብደብና መታሰር ምክንያት ለግዜው ቁሟል። ስብሰባው ግን ነገ ይካሄዳል።

ዓረና ፓርቲ ነገ እሁድ ከእንደርታ ህዝብ ጋር በኲሓ ከተማ ለሚያደርገው ህዝባዊ ስብሰባ ቅስቀሳ እንዳያደርግ ተከለከለ። ህወሓቶች ህዝባዊ ስብሰባ እንድናደርግ የፈቀዱልን ሲሆን ህዝቡን ለማሳወቅ ቅስቀሳ ማድረግ ግን አይፈቀድም አሉን። ህወሓቶችን ያስፈራ ጉዳይ የትግራይ አርሶአደሮች የብድር ብዝበዛ ያቀጣጠለው የህዝብ ተቃውሞ ነው። ቅስቀሳው ግን ይቀጥላል። ህዝብ አማራጭ ሐሳብ የመስማት መብት አለው። የህወሓት ዓፈና እንቃወማለን።

በሌላ በኩል ደቡብ ሕብረት-ኢሦዴፓ ፓርቲ ዛሬ ቅዳሜ መጋቢት 20, 2006 ዓም በሀዋሳ ከተማ ህዝባዊ ስብሰባ ጠርቷል። ዓረና ፓርቲም ተጋብዟል። የዓረና ተወካይ አቶ ካሕሳይ ዘገየ ንግግር ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል። ደቡብ ሕብረት -ኢሦዴፓ በደቡብ ክልል እንቅስቃሴ መጀመሩ የሚያኮራ ነው። የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ ፓርቲም በኦሮምያ ክልል ቅስቀሳ እንደሚጀምር ይጠበቃል።

Ze-Habesha Website may contain advice, opinions, and statements of various information and content providers. The Website neither represents nor endorses the accuracy of information or endorses the contents provided by external sources. All blog posts and comments are the opinion of the authors.

Print Friendly

Source Article from https://www.zehabesha.com/amharic/archives/13959

Post Comment